ብዙ ጊዜ እውነትን ውሸት ይቀድመዋል-የሺሃሳብ አበራ

ብዙ ጊዜ እውነትን ውሸት ይቀድመዋል፡፡ እውነት ዳተኛ ናት ወይም ቶሎ አትገለፅም፡፡ እውነት ቶሎ መገለፅ ባለመቻሏ ምክንያት በዓለም በስህተት ብዙ እልቂቶች ተፈፅመዋል፡፡
በቅርብ በሰው ልጆች የእስር በእርስ እልቂት ጥቁር መዝገብ ውስጥ፣የሚታወቀው የሩዋንዳው የቱትሲ እና የሁቱ ጎሳዎች ግጭት አንዱ ነው፡፡ የግጭቱ የወዲያው መንስኤ(immediate
cause) በነ ቤልጂየም ፍላጎት የሩዋንዳን ፖለቲካ የሚመሩት ሁቱዎች ነበሩ፡፡ የሁቱዎች የበቀለው የሩዋንዳው ፕሬዜዳንት ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ተገደለ፡፡ ገዳዮችም ቱትሲዎች እንደሆኑ የሁቱ መር ሚዲያዎች አስተጋቡ፡፡ የጅምላ ፍጁቱ ተጀመረ፡፡ በ100 ቀናት ውስጥ 70% የሚሆነው የቱትሲ ማህበረሰብ ተገደለ፡፡ ሁቱዎችም ስደትን መረጡ፡፡ ከግድያው በኃላ ሁኔታው ሲጣራ ከሁቲ ብሄር የተወለደውን የሩዋንዳውን ፕሬዜዳንት የተገደለው በሁቱ ተወላጅ በሆነ ሰው እንደሆነ ተረጋገጠ፡፡
የሩዋንዳ የእርስ በእርስ እልቂት የተፈፀመው በውሸት መቅደም እና በእውነት መዘግየት ምክንያት ነበር፡፡
….
መስከረም 2 ቀን 1967 ዓም ቀዳማዊ ሀይለስላሴ በበታች ወታደሮቻቸው ከዙፋናቸው ሲነሱ፣ ፊውዳል የተባለው ሁሉ ወደ እስር ሲወረወር፣ፀረ ለውጥ እየተባለ በደርግ ርሸና ሲካሄድ የአዲስ አበባ ወጣቶች ደርግን ተቃውመው ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ፡፡ ደርግ ሰልፉን ቀርፆ የአዲስ አበባ ህዝብ በዘውድ
አራማጆች ላይ የተወሰደውን እርምጃ አደነቀ ብሎ ገልብጦ ዜና አሰራው፡፡ የደርግን ዜና የሰማ የክፍለ ሀገር ሰውም እንደ አዲስ አበባ ህዝብ ለመደገፍ ተነሳ፡፡ ውሸት እውነትን ስለቀደመው ህዝቡ ደርግን ደገፈ፡፡ደርግ በውሸት ህዝባዊ ሆነ፡፡ በእውነት ሲገለጥ ግን የለየለት አምባገነናዊ ሆነ
……..
በ 1953 መፈንቀለ መንግስቱን የመራው መንግስቱ ሲያዝ፣ ከኪሱ ውስጥ ከ40 ዓመት በላይ የሆነው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይገደል ይላል ተብሎ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ተነበበ፡፡ ከ 40 ዓመት ዕድሜ በላይ ያለው ሁሉ መፈንቀለ መንግስቱን እያወገዘ፣ወጣቱን ትውልድ ተቸ፡፡ ዕውነታው ግን ራሱ መንግስቱም በወቅቱ የ44 ዓመት ጎልማሳ ነበር፡፡ የጃንሆይ ባለስልጣናት የፈጠሩት ፖለተቲካዊ ውሸት ነበር፡፡
….
በሴራ ፖለቲካ ትንታኔ፣ውሸት ለዓላማ እስከጠቀመ ድረስ ቅድስና ነው፡፡ይሄን ማኬቬሊም ይለዋል፡፡

የከሰሞኑ ሁኔታም ከዚህ የሚያልፍ ሃቅ አይኖረውም፡፡ መንግስት ጉዳዮን መጠነ ርዕዮን ለማሳደግ” የመፈንቀለ መንግስት ሙከራ” ብሎታል፡፡ ከባህርዳር እስከ አዲስ አበባ ያለውን መፈንቀለ መንግስት የመራው ጀኔራል አሳምነው ፅጌ እንዲሆን ተደርጎም እየተነገረ ነው፡፡
መንግስት ግዝፈት ሰጥቶ የመፈንቀለ መንግስት ነው፡፡
አድራጊውም ጀኔራል አሳምነው በማለቱ፡
1) ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ የኢትዮጵያ መንግስት የለየለት አምባገነን ሆኖ የማሰር እና የመግደል እርምጃ ቢወስድ እንኳ እንዳያማው አድርጓል፡፡ እስሩ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የእስሩ ምክንያትም በመፈንቀለ መንግስት ሙከራ መጠርጠር ስለሆነ
ለማሰር መንግስት ስሁታዊ የህግ መሰረት አግኝቷል፡፡
2) አማራን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ሆነ ከኢትዮጵያን ጋር ለመነጣጠል ተጠቅሞበታል፡፡
የጀኔራል ሰዓረ ገዳይ ብሎ የገዳዮን ስም አማራነት ለመናገር እስከ ቅድመ አያቱ መናገር ተገዷል፡፡ ከዛ ትምክህተኞች የሚል ዘፈን ተጀመረ፡፡ ከአሶሳ እስከ ምያሌ ያለ አማራ በአማራነቱ ታሰረ፡፡ እነ አምባሳደር ኸርማን ኮህንንም “መፈንቀለ መንግስቱ የአማራን የበላይነት ለማምጣት የታለመ ነው” ብሎ ከሴራው ጎን ቁሞ ታይቷል፡፡
3) የአማራ እና የትግራይን ህዝብ በማጣላት የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሙሉ በሙሉ ከሰሜን ወደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ መንጠቅ፡፡ ይህ አካሄድ የኩሽ ህዝቦችን ጥምረት ለማሳካትም አንድ እርምጃ ይሆናል፡፡
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በተለይም በኢህአዴግ በሞት መነገድ ተለማጅ የፖለቲካ ሴራ ነው፡፡ የመከላከያ አዛዡ ጀግናው ሃይሎም አርአያ በአንድ ኤርትራዊ ነጋዴ እንደተገደለ ተወራና የኤርትራ በጎ አመለካከት የነበራቸው አመለካክታቸው ልክ እንዳልሆነ በጀግናው ሞት ተነገራቸው ፡፡ የብሄራዊ ደህንነት ዳይሬክተሩ አቶ ክንፈ ገብረመድህን ተገሎ አቶ ጌታቸው አሰፋ ተተክቷል፡፡ የአዲስ አበባ የሽግግር መንግስቱ ከንቲባ አቶ ሙሉዓለም አበበ ተገሎ እነ ታምራት ላይኔ የብአዴን አውራ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ሌሎችም በርካቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተገለዋል፡፡ እነ ስየ አብርሃ ታስረው እነ አቶ መለስ ንጉስ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ በሞት እና በእስር ማትረፍ የኢህአዴግ ባህሪ ሆኗል፡፡ በቅርብ እንኳ ከሰኔ 16 ቱ የዶክተር አብይ የግድያ ሙከራ እና የአቶ ጌታቸው አሰፋ በገዳይነት መፈረጅ፣ ከዛም እውነቱ ያልወጣው የህዳሴው ግድብ እና የዳንጎቴ ሲሚንቶ ስራ አስኪያጆች ግድያ…..እነዚህ ሁሉ ተራ ዘፈቀዳዊ አይደሉም፡፡ የከሰሞኑ ግድያ የሚለየው መንግሥት
ገዳዮን ቶሎ ማሳወቁ ፣በተመሳሳይ ጊዜ የሟቾች መብዛት እና የግድያውን ግዝፈትም እስከ መንግስት ነቀላ መንግሥት ማድረሱ ነው፡፡
በፕሮፓጋንዳ የራስን እውነት ፈጥሮ ራስን አሸናፊ ለማድረግ የሚደረግ ማካቬላዊ ፖለቲካዊ ሩጫ ነው፡፡
ከሰሞኑ ያጣናቸውም ከጀኔራል አሳምነው እስከ ጀኔራል ሰዓረ፣ከአቶ ምግባሩ እስከ ዶክተር አምባቸው ለህዝባቸው ቀናኢ
እሳቤ የነበራቸው ግን ለሴራ ፖለቲካ መስዋዕትነት የቀረቡ የህዝብ ልጆች ናቸው፡፡
4) አማራን በገዳይ እና አስገዳይ አንጃዎች አቁሞ እንደ ዘመነ መሳፍንቱ ወደ አውራጃዊነት ቁልቁል ማውረድ፡፡ ይህ ሲሆን የአማራ ፖለቲካ ከወረዳ እና ከዞን ስለማያልፍ ማዕከላዊ መንግስቱ ሀገሪቱን ራሱ በሚፈልጋት መንገድ ለመስራት ይጠቀምበታል፡፡ የአማራን ምልክቶች በራሱ በአማራው እያስነቀለ አማራን ምልክት አልባ ማድረግ ግብ ሊሆን ይችላል፡፡ በመግቢያ እንደገለፅኩት ውሸት ከእውነት ስለሚቀድም፣በአማራ በተቃርኖ ጎን የቆመው አካል በውሸት ሊያተርፍ ይችላል፡፡

ስለዚህ ለእኛ አማራዎች፡
1) አራቱም ያጣናቸው የአዴፓ አመራሮች እኩል አማራዎች ናቸው፡፡ መሞታቸው ያመናል፡፡ ከሟቾች ወገን አንዱን ትልቅ አንዱን ትንሽ አድርጎ የልዮነት ወሰን መፍጠር ፈፅም አይገባም፡፡
ዶክተር አምባቸውም ሆነ ብርጋዴር አሳምነው እንደ የአቅም እና
ተሰጥኦቸው ለአማራ የሚችሉትን የሚያደርጉ ምስጉን
መሪዎቻችን ነበሩ፡፡ በግለሰቦች ዙሪያ እየተሰባሰቡ ከመቧደን
ይልቅ ፣ግለሰቦችን አንድ ያደርጋቸው ስለነበር ዓማራዊ
ዓላማቸውን እያሰብን፣ለአማራ ሊሰሩት ያሰቡትን ሁሉ ለመስራት መንገድ መጥረግ ያስፈልጋል፡፡ የገዳይ እና የአስገዳይ ተረክ እያወፈርን ከሄድን እንደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁሉ አማራ እርስ በእርሱ የማይታረቅ ህልም ሊኖረው ይችላል፡፡፡ የማይታረቅ ህልም ደግሞ አደገኛ ነው፡፡
2) አዴፓን ስንተችም ሆነ ስናሞግስ ስራዓታዊ መዋቅሩን እንጂ ግለሰቦችን ባይሆን፡፡ ግለሰብ ጎበዝም ይሁን ሰነፍ የስራዓቱ አገልጋይ ነው፡፡ የሰላ ስራዓት ካለ ሰነፉ ይጎብዛል፡፡በተቃራኒው አጎብዳጅ ስራዓት ከሆነ ደግሞ ምርጦችንም ስራዓቱ ሊያጎብጣቸው ይችላል፡፡፡ ግለሰብን እየለዮ መተቸት ወይም መቃወም ለስራዓታዊ ለውጥ አይጋብዝም፡፡ ከዚህ አዙሪት መላቀቅ አለብን፡፡
3) ጊዜ ምንንም ነገር ይወስናል፡፡ በዚህን ጊዜ አዴፓ እና አብንን በተለየ ሁኔታ መደገፍ ይሻላል፡፡ የብአዴን ፖለቲካዊ ስሪት ትናንት በህወሓት እንደተሰራ ሁሉ ዛሬ ደግሞ በሌላ አካል ከተሰራ የአማራን ትግል ውጤት ያርቃል፡፡ የከሰሞኑ ክስተት ዋነኛ ዓላማም ክልሉን ደካማ አድርጎ ታዛዥ አመራር እንዲፈጠር መሰረት ያደረገ ነው፡፡
….
እንደ ህዝብ የአማራ ህዝብ በሰሞኑ ክስተት ያሳየው መረጋጋት እና ጥሞና የሚደነቅ ነው፡፡ ዝምታ ከመናገር የበለጠ ጉልበት አለው፡፡ አማራ መንግስታዊ ህዝብነቱን አረጋግጧል፡፡ በዝምታው ሴራውን አምክኗል፡፡ ውስን የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች የሚያደርጉትን የዕርስ በዕርስ ገመድ ጉተታ ወደ ማህበረሰቡ ቢገባ ኑሮ ትምህርት ቤቶች ሁሉ እስር ቤት ይሆኑ ነበር፡፡ የአማራ ፖለቲካ እንደ ኢንግልስ ፍልስፍና “ከህዝቡ ወደ ልሂቃኑ መሻገር አለበት፡፡
የህዝቡን የእሳቤ ደረጃ ሊሂቃኑ ሊለምደው ይገባል” :: እንደ ማኬቬሌ” ህዝብ በሊሂቃን ይሰራል” የሚል ፍልስፍና ብንይዝ ኑሮ በአማራ ሊሂቃን ሽኩቻ የተሰራ ህዝብ አብሮነቱ ይላላ ነበር፡፡፡ እና ፖለቲካዊ ጥሞናን ከአማራ ህዝብ መማር ግድ ይላል፡፡ በጥሞና ውስጥ የአማራ በየዘርፉ ያሉ ምልክቶችን ለማጥፋት(ለማሰር) የሚደረግን ከበባ፣የአማራን እሴት የማጥፋት ሴራ ታዝቦ መፍትሄ መስራት ይቻላል፡፡
.
በዚህ ወቅት የምንሰራው ወርቃማ ስራም ሆነ፣ አጉል ስህተት እንደየባህሪው ታሪካዊ ሆኖ ይመዘገባል፡፡ የገዳይ እና የሟች አጃቢ በመሆን ብቻ ገዳይን ማንገስ፣ሟችንም ማስነሳት አይቻልም፡፡ ከሁለቱም ወገን ለአማራ ብሎም ለኢትዮጵያ ሊሰሩ ያሰቡትን መልካም ስራ እኛ እንስራላቸው፡፡ ድርጊቱ እንዳይደገም
መከባበር እና መናበብን የህይዎት ዘመን መርህ እናድርግ፡፡
….
ማንም እየተነሳ ለራሱ በሚመቸው እና በሚያተርፈው መንገድ የሚሰራው ፕሮፕጋንዳ ለአማራ አይጠቅምምም፡፡ እውነት አርፋጅ ቢሆንም ፈፅሞ መገለጡ ግን አይቀርም፡፡ ስተን ድርብ ፀፀት እዳናስተናግድ ለነገ አስበን ዛሬን እንስራው፡፡ ፖለቲካ ነገ ነው፡፡ ነገ የሚሰራው በሁነት እና በስሜት አይደለም፡፡ በተሻጋሪ ምክንያት ነው፡፡ ነገ በዛሬ ይደገፋል፡፡ ነፃነት እና ሰላም

ለተከበረው ለህዝባችን!!”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

x

Check Also

አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ትብብር ለአማራ

International Ethiopian Women’s Support for Amara www.ewointernational.org 1ethioamara@gmail.com ከአማራ ህዝብ ጎን እንቆማለን! በአማራው ህዝብ ላይ ...