ግልፅ ደብዳቤ ለአምባቸው መኮነን(ዶ/ር) | ወንድይራድ ሀይለገብረኤል

አማራ የህክምና ባለሙያ ዶክተሮች፡ ስፔሻሊስቶች እና ሳብ ስፔሻሊስቶች እየደረሰባቸው ባለው መጠነ ሰፊ በደል አስደንጋጭ ለሆነ ፍልሰት ተዳርገዋል። ሳይማር ያስተማራቸውን ወገናቸውንም በነፃነት ማገልገል አልቻሉም።
===

አምባቸው መኮነን (ዶር )
የአብክመ ርዕሰ መስተዳድር
ባህርዳር
——–

ግልባጭ:-

* ለአብክመ ጤና ቢሮ

* ለፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ሆስፒታል አስተዳደር

ጉዳዩ:– በአስቸዃይ ሊታረም የሚገባ ስህተትን ስለመጠቆም፡
—————–

በመጀመሪያ ደረጃ የሀገራችንም ሆነ የህዝባችን ዕጣ ፋንታ በእጅጉ እያሳሰበን መስተካከል አለባቸው ብለን የምናምንባቸውን ጉዳዮች ስንጠቁም በቀናነት ተቀብላችሁ የማስተካከል እርምጃዎችን ስለምትወስዱልን በህዝባችን ስም ምስጋና ማቅረብን እንወዳለን። የገጠመን ፈተና የትኛችንም በባይተዋርነት ቆሞ ለመመልከት ወይንም በጭፍን ተቃውሞ ለመጠመድ እድል አይሰጥም።
===

ለአብነት ለመጥቀስ ያክል ወንድማማች በሆኑት በአማራና በቅማንት ህዝቦች መካከል ስውር እጆች የለኮሱትን እሳት ለማጥፋት የአስቸዃይ ግዜ አዋጅ መጣል ስላለበት በተደጋጋሚ የጠየቅነው ጥያቄ መልስ አግኝቶ አንፃራዊ ሰላም መገኘቱን እናስታውሳለን። ለዚህም እናመሰግናለን!!

የቀረ ጉዳይ ቢኖር ያለህግ አግባብ በፓርቲ ውሳኔ የተደረገውን ሪፈረንደም ሙሉ በሙሉ ሰርዞ ደግሞ የማድረጉ ተግባር ህዝባዊ ፍላጎት ሆኖ ከተገኘ ህጋዊነትን በተላበሰ መልኩ እንደገና እንዲተገበር የማድረጉ ብርቱ ስራ ነው። ጥያቄው እላያችን ላይ የተጫነብን ቢሆንም ለግዜውም ቢሆን እየተገዛንበት ያለውን ህገ መንግስት የተመረኮዘ በመሆኑ አወንታዊ ተፈፃሚነት ያገኛል የሚለው ተስፋችን የፀና ነው።
===

ያለበቂ ቅድመ ዝግጅትና ስርዐት፡ ሀገሪቱ የምትገኝበትን ተጨባጭ ሁኔታ ባላገናዘበ መልኩ ሊደረግ ታስቦ የነበረውን የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ስለመሰረዝ የቀረበውን ፖለቲካዊና ሳይንሳዊ መረጃዎችን የተመረኮዙ በርካታ አቤቱታዎችን ግንዛቤ ውስጥ አስገብታችሁ ትክክልኛ የሆነ ውሳኔ መወሰናችሁንም እናስታውሳለን። ለዚህም እናመሰግናለን!!!
===

እራሳቸውን በአሸናፊነት ቆጥረው ሀምሳ ሚሊዮን አማራን ሆን ተብሎ ባገለለና ባላሳተፈ የፖለቲካ ሴራ እላያችን ላይ የተጫነብንን “ህገ መንግስት” አማራንም እንደዜጋ ቆጥሮ በአፅኖት መሻሻል ይገባዋል ስንል ያቀረብነውን መሰረታዊ ጥያቄ ተቀብላችሁ በቀዳሚ አጀንዳነት መያዛችሁን በማየታችንም ልናመሰግናችሁ እንወዳለን።
===

ዛሬም የተለመደው ጀሮአችሁ እንደማይነፈገን በመተማመን ተጨማሪ አቤቱታ ይዘን ቀርበናል። ይሄውም አጠቃላይ የክልሉን የጤና ቢሮና ብልሹ የሆነው የሆስፒታሎች አሰራር ባስቸዃይ እንዲታረም መጠየቅን ይመለከታል።

እንደሚታወቀው የአማራ ህዝብ አለማችን ላይ ከሚኖሩ ነገዶች በከፍተኛ ድህነትና የጤና ዕክል የሚኖር ህዝብ ነው። ችግሩን እንደአልጀዚራ የመሳሰሉት አለምአቀፍ የመገናኛ አውታሮች በሰፊው መዘገባቸውም ይታወሳል። “የተሟላ ጤና ሰብዐዊ መብት ነው” በሚል መሪ ቃል የሚንቀሳቀሰው የአለም ጤና ድርጅትም የአማራው ህዝብ ላይ የተጋረጠው የድህነት ልጅ የሆነው የጤና ችግር አሳሳቢ እንደሆነ ስጋቱን በተደጋጋሚ ጌዜ ገልጿል።
===

“ህዝቤ በዕውቀት ማነስ ጠፋ” እንዳለ ታላቁ መፅሀፍ ፡ በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙት ሆስፒታሎች አስፈላጊው የጤና ሳይንስ ክህሎት በሌላቸው ካድሬዎች መመራታቸው ለችግሩ መድለብ ቀዳሚው ምክንያት መሆኑን ማንም የሚስተው ጉዳይ አደለም። መፍትሄው በጣም ቀላል ነው። ካድሬዎቹን በክብር አስወግዶ ሆስፒታሎች በባለሙያዎችና በህክምና ዶክተሮች እንዲተዳደሩ ማድረግ ነው። ቀደም ተብሎ እንደተገለፀው ጤና ሰብዐዊ መብት ነው። የፖለቲካ ይሁንታ አያስፈልገውም። የፖለቲካ ካድሬዎች ከሆስፒታሎችና ጤና ቢሮዎች ገለል ይደረጉ። የህክምና ተቛማት በህክምና ባለሙያዎች ይተዳደሩ።
===

ለአብነት፡
———–

በፈለገ ህይወት አጠቃላይ ሆስፒታልና እና በክልሉ ጤና ቢሮው ከጤና ብቻ ሳይሆን ከጤነኛ ዕውቀት ጭምር የፀዱ ስራ አመራሮች በሚፈጥሩት ችግር ምክንያት የህክምና ባለሙያዎች አጥብቀው የደከሙበት ሆስፒታል የአገልግሎት ጥራቱና ደረጃው ሊገመት በማይችል መልኩ መውደቁን ለመጥቀስ እንወዳለን። አልፎ ተርፎም በርካታ ዶክተሮችና ስፔሻሊስቶች — “”ለምን ሆስፒታሉ የአገልግሎት ጥራቱን ማሻሻል አለበት ብላችሁ ጠየቃችሁ? ለምንስ ችግሩን በማህበራዊ ሚድያ አሰጣችሁት”” ተብለው በካድሬዎቹ በመከሰሳቸው የዩንቨርሲቲው ስፔሻሊስቶች እና ሳብ ስፔሻሊስቶችም ጭምር ሳይቀር “አትድረሱብን” ተብለው መታገዳቸውን የተመለከተ አስተማማኝ መረጃ ደርሶናል።
===

ለመሆኑ ሃገሪቱ በከፍተኛ ወጭ ከድሃ ገበሬ ላይ በተሰበሰበ ግብር ያስተማረቻቸው እነዚህ የደለበ ክህሎትና ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች “አትድረሱብን” ተብለው ገለል ከተደረጉ የማህበረሰባችን ጤና አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ሊጠበቅ የሚችለው በነማን ይሆን? በጣም ያሳዘነን ጉዳይ ነው። መፍትሄ በአስቸዃይ ይፈለግለት ስንል አቤቱታችን አቅርበናል።
===

እንዲህ የተበላሸ ስራ በመሰራቱ ሳቢያ በርካታ ታካሚ ወገኖቻችን ጥራቱን የጠበቀ ህክምና ስለማያገኙ ለከፍተኛ ዕንግልትና አላስፈላጊ ሞት ተዳርገዋል። በተጨማሪም ያለየሌለ ጥሪታቸውን በማሟጠጥ የተሻለ ህክምና ፍለጋ ወደአዲስ አበባ በመሄድ ለከፍተኛ ውጣ ውረድና ወጭ ተዳርገዋል።
===

በሙያቸው በመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ ወገናቸውን መርዳት ያልቻሉት የህክምና ዶክተሮችና እስፔሻሊስቶችም በግላቸው ክሊኒኮችን በመክፈት በተጨማሪ ሰዐትና በሙሉ ጊዜ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ቢሞክሩም በጤና ቢሮክራሲው ውስጥ በተሰገሰጉ ካድሬዎች ከፍተኛ ወከባ እየተፈፀመባቸው ይገኛል።
===

ጥቂት ሀኪሞች ከዕጅ ወደአፍ ከሆነችው ደመወዛቸው ላይ ቆጥበው ጥምረት እየፈጠሩ የከፈቷቸው ክሊኒኮችን የክልሉ ጤና ቢሮ እንደስትራቴጅክ አጋር ተመልክቶ ማበረታታትና ማጠናከር ሲገባው እንደጠላት ተቆጥረው እንዲዳከሙ ብሎም እንዲዘጉ እየተደረገ ነው። በመሆኑም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ስፔሻሊስቶች ክልላቸውን እየለቀቁ ወደአዲስ አበባና ወደውጭ ሀገራት አስደንጋጭ በሆነ መልኩ እየፈለሱ ነው።
===

ቀደም ብሎ በሙያቸውና በነፃነት ወገናቸውን ለማገልገል ባለመቻላቸው የተነሳ በስደት ተበትነው የሚገኙትን ሀኪሞች ሰብስበን በመመለስ ወገናቸውን እንዲታደጉ እናደርጋለን በሚባልበት በዚህ ወቅት በእጃችን የያዝናቸውን ዶክተሮችና ስፔሻሊስቶች ያለአግባብ እየበደሉ እንዲሰደዱ ማድረግ እጅግ የሚያሳዝን ክስተት ሆኖ አግኝተነዋል።
===

በመሆኑም የክልሉ መንግስት ጤና ቢሮ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድቶ ችግሩ የሚታረምበትን መፍትሄ በአስቸዃይ እንዲያስቀምጥ ስናሳስብ ርዕሰ መስተዳድር ዶር አምባቸው መኮነንም ለችግሩ ተገቢ ትኩረት ሰጥተው በአስቸዃይ እንዲስተካከል እንዲያደርጉ ትርጉም ያለው የህክምና ግልጋሎት አጥቶ ለከፍተኛ እንግልት፡ አካል ጉዳትና ሞት ተዳርጎ በሚገኘው ህዝባችን ስም እናመለክታለን።
===

ጥያቄያችን በአጭር ጊዜ ውስጥ መልስ አግኝቶ የህክምና ባለሙያወቻችንም ተገቢው ነፃነትና መብት ተሰጥቷቸው የካድሬ ይሁንታን ሳይሆን የሞያ ኢቲክስና ዲሲፕሊንን ተከትለው የህዝባችን ጤና አስተማማኝ በሆነ መልኩ እንደሚጠብቁ ተስፋችን ፅኑ ነው።

እናመሰግናለን!!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

x

Check Also

ብዙ ጊዜ እውነትን ውሸት ይቀድመዋል-የሺሃሳብ አበራ

ብዙ ጊዜ እውነትን ውሸት ይቀድመዋል፡፡ እውነት ዳተኛ ናት ወይም ቶሎ አትገለፅም፡፡ እውነት ቶሎ መገለፅ ባለመቻሏ ምክንያት በዓለም ...