የራያ ህዝብ አሳሳቢ ህልውና ችግር -በለጠ ሞላ

ሰሞኑን ራያን የተመለከተ እጅግ የሚያሳዝን ዜና ነው የሰማነው!

በርግጥ ይህ ለራያ ህዝብ የተለመደ ጉዳይ ሆኗል። በዚህ መልክ የሚመጣው ሀዘን ብዙ ቤተሰብን አድርሷል፤ የኔም ሁለት የአጎቴ ወጣት ወንድ ልጆች (ትንሽና ትልቅ) በዚህ መልኩ ህይወታቸውን አጥተዋል። ባህር የበላውን የራያ ወጣት ቁጥር ፈጣሪ ይወቀው።
——————-
መሬትማ ነበር….ሰፊና ለም መሬት! ወጣቱ ሀገሩን እየለቀቀ ሲሰደድ መሬቱን ሌላ ያዘበት እንጅ የሚታረስማ ለም መሬት አልጠፋም ነበር!
እንዲህ ነው….
ራያ ቆቦ ላይ ከብት እየጠበቅን ያደግንበት እጅግ ሰፊ ጥቅጥቅ ደን (Equatorial rain forest) ነበር። አቧሬ ይባል ነበር። ይሄም ደን በውስጡ ብዝሀ ህይወትን አቅፎ ይዞ ይገኝ ነበር። በርካታ ተሳቢወች፣ አጥቢወችና አእዋፍ በውስጡ ይገኙ ነበር…..ሀብታም ደን ነበር!!
በዚህ ደን ላይ የብዙ ቤተሰብ ህይወትም ተመስርቶ ነበር። የአካባቢውም ስነምህዳርን ከመጠበቅ ባለፈ የአካባቢው የቁም ከብት ህይወታቸው በዚሁ ጥቅጥቅ ደን ላይ እንዲሁ የተመሰረተ ነበር።
በ1990/91 ላይ ለኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ከኢትዮጵያ በኩል ዝግጅት ሲደረግ የትግራይ ምልምሎች በዚህ ደን ውስጥ በግዜው በተቋቋመ ሰፊ የማሰልጠኛ ማእከል ነበር የሰለጠኑት። ታዲያ የህወሓት ባለስልጣናት ይህን ግዜ ደኑን በደንብ አወቁትና ለወደፊት ጥፋትን ደገሱለት! በ1998 ዓ.ም ከኢትዮ ሱዳን ድንበር ጋር ተያይዞ ዘለቀ እርሻ ልማት የተባለ የብአዴን ድርጅት ከመተማ አካባቢ ተነስቶ ቆቦ ትራክተቶቹን አሰፈረ። አባቶቻችንን ሰብስበው “ደኑን መንጥረን ሰብል ልናለማበት ነው፣ ደን ከሆነ የምትፈልጉት ተራራውን ሁሉ እናለማዋለን” በማለት ህዝቡን ዝም እንዲል አዘዙ። ህዝቡም ዝም አለ። ሰፊውን ደን መንጥረው ግንዱን አግዘው ለመጨረስ 5 አመት ወሰደባቸው ግንዱም በትራንስ ኢትዮጵያ ትራከሮች በየቀኑ እየተጫነ ለማይጨው ችፕውድ ፋብሪካ ግብአት ዋለ። 2003 ላይ ምንጠራው በሙሉ ተፈፀመ!!
—————
ብዙ ሄክያር (ለግዜው በውል አላውቀውም) በዘለቀ እርሻ ልማት ስር ሆኖ አደንጓሬና ወደአክር የምትባል የራያ ሰው “የድሀ እህል” የሚላትን የማሽላ አይነት ማምረት ጀመረ፤ አባቶቻችንም “የወደአክር ልማት” ሲሉ የዘለቀ እርሻ ልማትን እንቅስቃሴ በትችት ሸነቆጡ።
ከዚህ የተረፈውን ሰፊ መሬት የአዜብ መስፍን ቤተሰብ የሆነ ሰው በአያሌው ጎበዜ ፈቃጅነት ሰፊ መሬት ወሰደና አትክልት አለማበት። ከዚህ የተረፈውን ደግሞ ከዩኒቨርሲቱ ተመርቀው ስራ ለሚፈልጉ ወጣቶች ለ14 እያደራጁና የሜቴክ ትራክተር በብድር ውል እያስፈረሙና የዲግሪያቸውን ኦርጅናል መያዣ እያደረጉ የእርሻ መሬት ሰጡአቸው….ግን ግን ትራክተሩም አልቆየምና ተሰበረ የትምህርት ማስረጃቸውም በመያዣነት እስከዛሬ ቆየ! ወጣቶቹም ፍሬአቸው ድካም ብቻ ሆነ እንጅ አንዳችስ እንኳ አላተረፉም!
አምና በጥር 2010 በተደረገው የቆቦ ወጣቶች/ህዝባዊ አመፅ ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት ውስጥ ዘለቀ እርሻ ልማት አንዱ ነበር….ንብረት ወድሟል ትራክተሮችም ተቃጥለዋል። ወጣቱም በቁጭት “የህዝባችንን መሬት ተቆጣጥሮ ወጣቱን እንዲሰደደ የሚያደርግ የወያኔ ድርጅት” በማለት ነበር እርምጃውን የወሰደው።
————-
ታዲያ የራያ ወጣት ባይሰደድ ምን ይደንቃል?!
ለወጣቱ የሚሆን ዛሬም ሰፊ መሬት አለ፣ በስፋት ጥቅም ላይ የሚያውላቸው አካል ቢኖር የራያ መሬት በርካታ ወንዞች አሉት፣ ገበሬው በገፍ ሽንኩርት ያመርታል ግን ደግሞ የሚገዛው እያጣ ምርቱ ይበሰብሳል። አለያም ለረጅም ግዜ አንድ ቁና ሽንኩርት በ5 ብር ከሰሜን በኩል ለሚመጡ ጅምላ ጫኞች እንዲያቀርብ ይዋከብ ነበር….በዚህም ስራ የያኔው ዘመን የአስተዳደር መዋቅር ውገናው ለገዛ ህዝቡ ሳይሆን ለጉልበተኛቹ ነበርና ለህዝቡ ጥቅም ሳይቆም ኖረ። አንዱ ሰሜናዊ ነጋዴ ጨረታ አሸነፈ ተብሎ የገበሬወቹን ሽንኩርት ጭኖ ከወሰደ በኋላ ክፍያ ሳይፈፅም የውሀ ሽታ ሆኖ ቀረ። ገበሬወቹም ይህንን ውል ላመቻቹት የወረዳው አንዳንድ ሰወች ጉዳዩን እልባት እንዲሰጧቸው ቢወተውቱም መልስ ሳያገኙ ቀሩ….ቢከሱም እንኳ በዳያቸው 800,000 ብር ክፍያ ሳይፈፅም መቀሌ ገብቶ ቀረ።
ገበሬወቹ ቲማቲምም ያመርታሉ ግን ብዙ ግዜ ይበሰብስባቸዋል። እንዴት አድርገው ምርታቸውን ለገበያ ማቅረብ እንዳለባቸው ስልጠና የሚሰጣቸው አካል ቢኖርና ይህንንም ማስተባበር ቢቻል ብዙ ህይወት በተለወጠ ነበር። በእነዚህ ዙሪያ ቴክኖሎጅውን አስገብቶ ስራ ቢሰራ የተወሰነ ውጤት ማምጣቱም አይቀርም ነበር።
ይህ ሁሉ ምክንያት ተዳምሮ ወጣቱን ወደ አረብ ሀገር እንዲመለከት አድርጎታል።

እስከማውቀው ድረስ በባህር ከሚሰደዱት ውስጥ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሳለ የትምህርት ማስረጀቸው በሜቴክ የተያዘባቸው ወጣቶችም ጭምር ይገኙበታል።
ለውጥ አለ ተብለናልና ዛሬስ በማን እናመካኝ ይሆን!?
የወገኖቻችንን ነፍስ ይማርልን!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

x

Check Also

ብዙ ጊዜ እውነትን ውሸት ይቀድመዋል-የሺሃሳብ አበራ

ብዙ ጊዜ እውነትን ውሸት ይቀድመዋል፡፡ እውነት ዳተኛ ናት ወይም ቶሎ አትገለፅም፡፡ እውነት ቶሎ መገለፅ ባለመቻሏ ምክንያት በዓለም ...