በኮሚኒስት እሳቤ ተተብትቦ ያደገው የኢትዮጵያ ፖለቲካ-የሺሃሳብ አበራ

በኮሚኒስታዊ እሳቤ ተተብትቦ ያደገው የኢትዮጵያ የፖለቲካ መንፈስ በአንድ ገፁ አሻጥር በሌላ ገፁ ደግሞ በገሃዱ ዓለም የሌለ ትወና የተጠናወተው ሆኖ አልፏል፡፡
በተለይ ለብሄርተኞች እጁን የሰጠው የአንድነት ፖለቲካ ከሀሳብ ማለፍ እንዳይችል ሆኖ ህዝቡን በምናብ እንዲነዳ አድርጎታል፡፡ የዜግነት ፖለቲካ መተግበር አይችልም እንጂ ከተተገበረ መልካምነቱ አያጠራጥርም ፡፡ ነገር ግን በሴራ እና በማስመሰል የተሞላ እና መሬት ላይ ያለውን ሀቅ ያልተረዳ በመሆኑ ድል አይቀናውም፡፡ ሁሌም ተንበርካኪ ነው፡፡ ውጤት ተኮር አይደለም፡፡

ሳይስማማ ቅንጅት ተፈጥሮ በ 97 የአንድነት ፖለቲካው የተሻለ ቅቡልነት ለጊዜው ቢያገኝም መልሶ ተዳፍኗል፡፡ ለመዳፈኑ መንስኤ ከኢህአዴግ ሴራ ባሻገር የራሱ መርህ አልባ ጥምረት እና አሻጥር ነው፡፡ እነ ልደቱ አያሌው እንደ ካሃዲ ተቆጥረው ሌሎች የገነኑበት አሻጥር በራሱ በጊዜ ሂደት ይገለፃል፡፡ ኢሳያስ አፈወርቂ በ 2015 ከOmn tv ጋር ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ ሁለት ስህተቶች ተሰርተዋል ይላሉ፡፡ አንደኛው በ 1983 ህዋኃትን የበላይ እንዲሆን ሻዕቢያ ማመቻቸቱ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በምርጫ 97 ቅንጅት ፓርላማ አለመግባቱ ነው፡፡ ቅንጅት ፓርላማ ገብቶ አዲስ አበባን ቅንጅት መርቷት ቢሆን የኦሮሞ ዋና ከተማ ከአዳማ አይነሳም ነበር፡፡ አዲስ አበባ ከዛሬው አጣብቂኝ ውስጥ አትገባም ነበር፡፡

አሁን እነ ግንቦት ሰባት የአዲስ አበባን ጉዳይ ዘንግተዋል፡፡ የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኝ መጀመሪያ ዋና ከተማ ሊኖረው ይገባል፡፡ ዋና ከተማ የሀገር መልክ ነው፡፡ የአዲስ አበባን ፖለቲካ ትቶ በዚህን ወቅት ወደ ገጠር መውረዱ ልክነት አይኖረውም፡፡ ግንቦት ሰባት ባለፈው ባህርዳር ላይ መሰብሰብ አልቻልኩም ብሎ ቅሬታ አቅርቧል፡፡ ማቅረቡ ልክ ነው፡፡ ግን የአቀራረቡ ሁኔታ ግን በደጋፊዎቹ በኩል አማራ ጠል ትርክት ተስተውሏል፡፡ ዶክተር ብርሃኑ ጉራጌ ስለሆኑ ተቃውሞ ገጠማቸው ምናምን እያሉ ሲለጣጥፉ ከርመዋል፡፡ ብሄርተኝነት የሚያወግዘው ግንቦት ሰባት ከኦነግ ክንፍ ከሆነው ጋር ከኦዴግ ጋር ፣ከሶማሊያ እና ከትግራይ የብሄር ፓርቲዎች ጋር ተስማምቶ ሲሰራ ከርሟል፡፡ ቢሰራም ግን ከአማራ ክልል ውጭ የትም መሄድ አልቻለም፡፡ በአዲስ አበባ ጉዳይ እንኳን ግልፅ አቋሙን ማሳየት አልቻለም፡፡

ግንቦት ሰባት በራሱ በተቃርኖ የተሞላ ንቅናቄ በመሆኑ አርበኞች ግንባር ፍታኝ እያለ ሁለት ጊዜ መግለጫ አውጥቷል ፡፡ የራሱን ውስን ሰራዊትም በትኗል፡፡ በዚህም እነ ነኣምን ዘለቀ ከድርጅቱ ራሳቸውን አግለዋል፡፡ ግንቦት ሰባት ሴረኛ እንደሆነ እነ ዘመነ ካሴ እና እነ መንግስቱ ወልደስላሴ በሚዲያ ተናግረዋል፡፡ አቶ ልደቱም ከግንቦት ሰባት ጋር ቀርቤ ልወያይ ብሎ ምላሽ አጥቷል፡፡ ስለዚህ ግንቦት ሰባት ሴረኛ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ አለመሆኑን ቀርቦ አልገለፀምና፡፡
..
የኦነግ ሰራዊት 17 ባንክ የዘረፈው፣ወለጋም በአስቸኳይ አዋጅ ውስጥ የወደቀው ለሰራዊቱ ድጋፍ ስላልተደረገ ነው፡፡ ኦነግ ተደራድሮ ሰራዊቱን የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ አባል አድርጓል፡፡ ግንቦት ሰባት ግን የራሱን አባሎች በትኖ በጠላትነት የፈረጀ ይመስላል፡፡ ግንቦት ሰባት በብዙ ጉዳዮች ዝምታን ከመረጠ በኃላ በራሱ አባሎች በተነሳ የእርስ በእርስ ግጭት መግለጫ አውጥቷል፡፡ የራሱን ችግር ቀድሞ ሳይፈታ የአማራን ወጣት እና የባህርዳር ከተማን መልካም ስም አጠልሽቷል፡፡ ባህርዳርን የብጥብጥ ማዕከል አስመስሎ ለአማራ ጠሎች ግባት ሆኗል፡፡ ወጣቱን እና አዴፓን እያነጣጠለው ነው፡፡ የአማራን ፖለቲካ ከሳሎን እንዳይወጣ በእርስ በእርስ ሽኩቻ እንዲወድቅ እያደረገው ነው፡፡ አዴፓ ጉዳዮን ሊያጤነው ይገባል፡፡

ግንቦት ሰባትም መጀመሪያ የራስህን የፖለቲካ ተቃርኖ ፍታ፡፡ አማራ ጠል ትርክትን ካላስወገድክ፣የአማራን ጉዳይ አጀንዳ ካላደረክ ወደ አማራ መምጣትህስ ምን ያደርጋል?! በግንቦት ሰባት ስም ብዙ የአማራ ወጣቶች ሙተዋል ፡፡ታስረዋል፡፡ ተስፋ ቢስ ሆነዋል፡፡ በኤርትራ የሞቱት አስከሬናቸው እንኳ አልመጣም፡፡ ግንቦት ሰባት በእሱ ስም ስለታሰሩት እንኳ ብዙ አልጮኸም፡፡ በዚህም የአማራ ህዝብ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል፡፡


አማራን ጠልቶ በተነሳው ፖለቲካ ምክንያት ብዙዎች ተፈናቅለው ለመርዳት ርብርብ እየተደረገ ባለበት ወቅት አንተ ስለ ዜግነት ፖለቲካ ታወራለህ?! ቤት ሲፈርስ፣ሲፈናቀል ዝም ትልና ሰላም ሲሆን ፖለቲካ ትቀሰቅሳለህ፡፡

በዚህን ወቅት የአማራ አንድነትን መፈታተን አማራን ለባርነት መዳረግ ነው፡፡ ሀገር ፈርሶ እየተሰራ አማራ እርስ በእርሱ ከፈረሰ በአማራ ህልውና ላይ የምትሰራ ሀገር ይፈጠራል፡፡
..
በአማራ አንድነት ላይ ይሄ ትውልድ አይደራደርም፡፡ ከተደራደረም ለሽንፈት ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

x

Check Also

ብዙ ጊዜ እውነትን ውሸት ይቀድመዋል-የሺሃሳብ አበራ

ብዙ ጊዜ እውነትን ውሸት ይቀድመዋል፡፡ እውነት ዳተኛ ናት ወይም ቶሎ አትገለፅም፡፡ እውነት ቶሎ መገለፅ ባለመቻሏ ምክንያት በዓለም ...