አዴፓ ወንበሩን ቢያገኝም በትክክል አይጠቀምበትም | የሺሃሳብ አበራ

ከ 2004 እስከ 2007 ዓም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሴት መምህራን ቁጥር ለመጨመር በሚል ከየትምህርት ክፍሉ በየዓመቱ አንድ ሴት መምህር ትቀራለች፡፡ ከትምህርት ክፍሉ 300 ተማሪዎች ኑረው አንድ ሴት ተማሪ ብትኖር እና ውጤቷ 2.0 ቢሆን 4.0 ያመጣው ወንድ ሳይቀር እሷ መምህር ትሆናለች፡፡ 2.0 ያመጣችው ሴት ከሁለት ዓመት በኃላ 4.0 ላመጣው ተማሪ ማስተሩን ሲማር መምህሩ ትሆናለች፡፡ያው መምህርነትም የፖለቲካ ውሳኔ ነውና፡፡ከዚህ የከፋው ደግሞ ከአናሳ ብሄረሰቦች በማለት ምንም ያምጣ ምን የዮኒቨርስቲ መምህር ማድረግ ነበር፡፡ ባጋጣሚ ከክፍሉ ዝቅተኛ ያለው አናሳ ከሚባል ብሄር የተወለደ ካለ መምህር ይሆናል፡፡ መምህርነት ሹመት እስኪመስል ድረስ በችሎታ ሳይሆን በፓለቲካ ምርጫ ስለነበር የከፍተኛ ትምህርት ተቋም እየሞተ ነው፡፡ ሴቶችንም ሆነ የአናሳ ብሄር ተወላጆችን እንዲማሩ የተሻለ ዕድል መክፈት እንጂ ሴት ወይም እዛ ስለተወለዱ ብቻ መምህር አድርጎ መሾም በትውልድ ላይ መፍረድ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ትምህርት ሚኒስቴር ስኬቴ ብሎ የሚገመግመው በከፍተኛ ተቋማት ውስጥ የሴት መምህራንን ቁጥር ጨምሬያለሁ እያለ ነው፡፡ለማስተማር ልዮ ዕድል ሰጥቶ ቢጨምር መልካም ነበር፡፡እኩል ከወንዶች ጋር አስተምሮ መምህር አድርጎ መሾም ግን ሙያን መግደል ሆኖ በተግባር ታይቷል፡፡

የዶክተር አብይ አስተዳድርም ከሩዋንዳ ቀጥሎ ሴት ሚኒስትሮችን በማብዛት ከዓለም መሪ ሆኗል፡፡ በጣም ጥሩ ነው፡፡ለፕሮፖጋንዳም ይመቻል፡፡ ዋናው ግን እነዚህ ሴት ሚኒስቴሮች ከወንዶች የተሻሉ ናቸው ወይ የሚለው ሲሰላ አትራፊ ከሆነ ነው፡፡ የዲሞክራሲ ቁንጮ የሆነችው አሜሪካ ሴት ባለስልጣን ብዙ የላትም፡፡የማይኖራትም አምባገነንን ሆና ሳይሆን መመዘኛው ችሎታ ስለሆነ ነው፡፡ምናልባት የኛ ሃገር ሴቶች ከአሜሪካ ሴቶች ልቀው፣ከወንዶችም ብዙ የተሻሉ ከሆኑ በፖለቲካ የታመመችቱን ሃገር ለማከም መፍትሄ ይሆናል፡፡ ችግሩ እንደ ሴት የዮኒቨርስቲ መምህር ምርጫ ለፖለቲካ ፖሮፖጋንዳ ፍጆታ መሙያ ከሆነ ነው፡፡

አዴፓም ሁለት ወንዶችን መልሶ ሁለት ሴቶችን አሹሟል፡፡ዶክተር አምባቸው መኮንን እና አቶ መላኩ አለበል ወርደው ዶክተር ሂሩት ካሳው እና ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ወደ ፊት መጥተዋል፡፡

ዶክተር አምባቸው መኮንን የሃገሪቱ ርዕሰ ብሄር ይሆናሉ፡፡ዶክተር ሙላቱ በዶክተር አምባቸው ይተካሉ፡፡ ዶክተር አምባቸው ማይክ ይዞ ፖለቲካ ከመናገር መቀስ ይዞ የምርቃት ሪቫን ወደ መቁረጥ ይሸጋገራሉ ማለት ነው፡፡ ዶክተር አምባቸው የአዴፓ ስራ አስፈፃሚ ናቸው፡፡ ፕሬዜዳትነትን እንዴት እንደመረጡት ግራ አጋቢ ነው፡፡ በእርግጥ ብዙዎች የአዴፓ መሪዎች ታክቷቸዋል፡፡ማረፍ ይፈልጋሉ፡፡ዶክተር አምባቸውም እረፍት ፈልገው ይሆናል፡፡ አቶ ደመቀም እረፍት ፈልገው ነበር፡፡እረፍት መሰጠት ነበረባቸው፡፡አቶ ደመቀ ስልጣን ለቀው ቢሆን አዴፓ ሌላ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ይኖረው ነበር፡፡ አዴፓ አቶ ደመቀን ለማንሳት ያደረገው ጥረት መልካም ነበር፡፡
……….
አቶ መላኩ አለበል አቶ ብናልፍን ሊተኩ ይችላሉ፡፡አቶ ብናልፍ ደግሞ ወይዘሮ ሙፍሪያትን ከሚልን ወይም ሌላ የአፈጉባዔነት መሰል ቦታ ያለበትን አካባቢ ሊይዙ ይችላሉ፡፡ ወይም በሌላ ዘርፍ፡፡ ዞሮ ዞሮ አቶ ብናልፍ ይለቃሉ፡፡
….
ብአዴን(አዴፓን) አቶ ደሴ ጥላሁን(የዝማምን ቦታ)፣አቶ እዘዝ ዋሴ(የአቶ ምግባሩን ቦታ) እና አቶ ምግባሩ ከበደ(የተስፋየ ጌታቸውን ቦታ ) ይዘው መምራታቸው አይቀርም፡፡
….
አዴፓ ከፌደራል ተቋማት ሁነኛ ቦታ አልያዘም፡፡እንዳይዝ ያደረገው ዶክተር አብይ አይደለም፡፡ራሱ አዴፓ ነው፡፡አዴፓ ሚኒስተሩን የድርሻውን የመምረጥ ሙሉ ዕድል ነበረው፡፡ዕድሉን ግን በትክክል የተጠቀመበት አይመስልም፡፡
….

አዴፓ ወንበሩን ቢያገኝም በትክክል አይጠቀምበትም፡፡

አዴፓ ራስነት(self) ስለሌለው ብዙ ለወከለው ህዝብ አይሆንም፡፡ብሄራዊ ባንክን፣ብሄራዊ ደህንነትን እና ኢንሳን አዴፓ ይዟል፡፡ ቢይዝም ግን ሃላፊዎቹ ብሄርተኛ ስላልሆኑ ለአማራ ብዙ አይጠቅሙም፡፡ወንበራቸውን ብቻ ያገለግላሉ፡፡ ዋናው ደግሞ ስልጣንን መጠቀም ነው፡፡ ኦዴፓ ጠቅላይ ሚኒስትርነትን ፈለገ፡፡አገኘው፡፡ስልጣኑን ተጠቀመበት፡፡ ጌታቸው አሰፋ ብሄራዊ ደህንነትን ይዞ ሃገሪቱን አሾራት፡፡ የአዴፓው ግን ያን አያደርግም፡፡ Related image
….
አንድ የትህነግ ባለሙያ ለትግራይ የሚያደርገው አንድ የአዴፓ ሚኒስትር ለአማራ ከሚያበረክተው ይበልጣል፡፡

አዴፓ ከራሱ ስንፈት ባለፈ የሚመራው ህዝብ ለአማራነቱ የቆመ ባለመሆኑ አዴፓ ራስ እንዳይኖረው ሆኗል፡፡ አማራው እኔ አማራ ነኝ ፡፡በኢትዮጵያ ውስጥ በአማራነቴ የሚገባኝ ጥቅም ላግኝ ብሎ አማራው ብዙ አይጠይቅም፡፡ አማራው ኢትዮጲያዊነቴ ይከበርልኝ ማለት ያበዛል፡፡መሪም ከህዝብ ይፈጠራልና አዴፓም አማራው ይጠቀም ከማለት ይልቅ ኢትዮጵያ ብሎ ይዋኛል፡፡ የአማራ ፖለቲካ የአሁኑን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ምት የዋጀ አለመሆኑ አማራውን ጎድቶታል፡፡

ኦዴፓ የአዲስ አበባን ከንቲባነት ፈለገ፡፡ፈልጎ ሲያገኝ ስልጣኑን ተጠቀመበት፡፡ አማራው ጠይቆ አዴፓ ከንቲባ ቢሆን አዲስ አበባ ላይ ለአማራ የሚጠቅም ስራ የመስራት ዕድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡
…..
ትግራይ፣ኦሮሞ፣ሲዳማ፣ሶማሌ የራሳቸውን ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ፈጥረዋል፡፡አማራ በማህበረሰብነት ሳይሆን በግለሰብነት ደረጃ ላይ ቁሟል፡፡የቡድን ፖለቲካ ገና አልተዋጠለትም፡፡ ባይዋጥለትም ግን ቡድንተኛ ባለመሆኑ ዋጋ ይከፍላል፡፡
….
አዴፓ ብሄርተኛ ባለመሆኑ አማራነት መሰባሰቢያ መሃሉ አይደለም፡፡ከአማራነት ይልቅ አካባቢያዊነት ያጠቃዋል፡፡ ሰሜን እና ደቡብ ወሎ፣ምስራቅ እና ምዕራብ ጎጃም፣ደቡብ እና ሰሜን ጎንደር እያለ በየአካባቢው ሲሻኮት የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሽቶ ይነጋል፡፡ብሄርተኛ አለመሆን አንዱ እዳው ጎጠኝነትን ማንገሱ እና ግለሰባዊነትን ማወፈሩ ነው፡፡ አዴፓ በዚህ ቅንፍ ውስጥ ታጥሯል፡፡ስለ አማራ ፖለቲካ እና ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ከመወያየት ይልቅ ስለ ደቡብ ጎንደር፣ስለ ምስራቅ ጎጃም፣ስለ ደቡብ ወሎ የፖለቲካ ሰንሰለት የሚፈትለው ይበዛል፡፡ በመሆኑም አዴፓ ከቀየው ሳይወጣ ከአዲስ አበባ ፖለቲካ እየኮበለለ እትብቱ ወደ ተቀበረበት መንደር መትመም ጀምሯል፡፡ አዴፓ ገጠር ወዶ ቀረ፡፡ እንዳይቀር አማራነትን ማጎን ነበረበት፡፡ ጎጠኝነት የፖለቲካ መጨንገፍን(political dwarfism) ያስከትላል፡፡ ለጎጠኝነት መስበሪያው ደንበኛ ብሄርተኝነት ነው፡፡ ብሄርተኛ ስትሆን ማዕከላዊ ሃሳብህ አማራ ይሆናል፡፡ጎጥህ አይሆንም፡፡ግለሰብነትህ አይሆንም፡፡

x

Check Also

Team Ambachew – ሚኪ አማራ

perfect leader ማግኘት አንችልም ነገር ግን እኛ ፐርፌክት ማድረግ እንችላለን፡፡ አሁን ተወደደም ተጠላም ዶ/ር አምባቸዉ ...