የአቶ ንጉሱ ንግግር- ወንድይራድ ሃ/ገብርዔል | ከግዮን መገናኛብዙሃን ማዕከል GMC

“….የአማራ ህዝብ ወንድም ከሆነው የኦሮሞ ህዝብ ጋር በኦሮምያም በአማራም ተሰባጥሮ በመኖሩ ምክንያት …  (ይደገም! … ይደገም! … ይደገም! ሲል ታዳሚው በፍተኛ ድምጽ ጩህቱን አስተጋባ …. አቶ ንጉሱም ደገሙት!) … የአማራ ህዝብ ወንድም ከሆነው የኦሮሞ ህዝብ ጋር በኦሮምያም በአማራም ተዋህዶ … ተዋልዶ … ተጋምዶ የሚኖር ህዝብ በመሆኑ ይህንን ገመድ በማጥበቅ … አንድነትን በማጎልበት ታላቅ ሃላፊነት ይዞ የመጣ ሚዲያ መሆኑን በመገንዘብ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እና የአማራ ህዝብ ከኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) ጋር ለመሰራት በእጅጉ ፍላጎት ያለን በመሆኑ ህዝባችንን እንድታስተሳስሩ … ህዝባችንን ከሌሎች መሰል ሚዲያወች ጋር ሰለፍቅር … ሰለአንድነት እና ሰለአብሮነት አብራችሁ እንደትሰሩ አደራ እያልኩ በድጋሜ እንኳን ለአገራችሁ ምድር አበቃችሁ እላለሁ …”  …. አቶ ንጉሱ ጥላሁን (በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የህዝብ ግንኙነት ጉዳይ ሃልፊ) 

========================================================================================================

አቶ ንጉሱ ይህንን የተናገሩት በጅዋር መሃመድ ስራአስኪያጅነት የሚመራው የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ OMN ሃገር ውስጥ ገብቶ ለመንቀሳቀስ ይፋዊ እወጃ ባደረግበት ታላቅ መድረክ ላይ ነው። ዝግጅቱ ላይ በርካታ ታዳሚዎች በመገኘት ለ OMN ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል። ለስራአስኪያጁ ለጀዋርም ያላቸውን ክብር ገልጸዋል። ጅዋርም ባዙቃውን (sliver apple laptop) ለአቶ ለማ መገርሳ በእግዝቢትነት አስረክቧል። መድረኩ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ኦሮሞነት የገነነበት እንደነበር አዳራሹ ውስጥ በእያንዳንዱ ታዳሚ ይወለበለቡ የነበሩት የኦነግ ባንዲራወች በቀዳሚነት ያስረዳሉ። ከአቶ ንጉሱ እና አልፎ አልፎም ከመድረክ መሪው በቀር አማርኛ ቋንቋ ሲነገር አለመደመጡም ዝግጅቱ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ብቻ ግንዛቤ ውስጥ ሰለማስገባቱ ሌላኛው ምልክት ነው። ትላንትና ያየሁት ሁኔታ አንድ ነገር አስታወሰኝ። …..የሳሙየል ቤኬት “አምላክን ጥበቃ”።  “ሁሉም በየራሳቸው ቋንቋ እና ስሜት ሰርክ እየተነጋገሩ … አንድም ቀን ሳይገባቡ … ፈጣሪያቸውን አግኝተው የእውንተን ሚስጥር ለመረዳት እየጠበቁ ለዘመናት ሲጠብቁ ኖሩ። በእንዲህ ሁኔታ እያሉ አንዳቸው-ካንዳቸው ሳይግባቡ … የፈጠራቸው አምላክም ሳይመጣ … በፈጣሪ ዘንድ ብቻ ትገኛለች ብለው የሚያምኗትንም እውነት ሳያገኟት እንደባዘኑ የቀሩት እነ ቭላድሚር እና እስትራጎን የተባሉት የሳሙኤል ቤኬት የብእር ልጆች ትዝ አሉኝ”  “waiting for Godot” (Samuel Beckett: 1952). እንግዲህ የኛ ነገር “Dance first. Think later. It’s the natural order” እንደተባለው “የእለት የእለቱን እንደጓያ ነቃይ እየገፉ ማየት ነው”። ትላንትና አቶ ለማ  በኦሮምኛ “ ቄሮ ራያ … ኦሮሞ ራያ” ሲሉ የሰሙ አማሮች …. “የወላዲት አምላክ ያለህ! … ራያ የኦሮሞ ነው አደለም የሚለው?” እያሉ አገር ይያዝ ሲሉ አየውና …. ምርር ብየ … ምነው ኦቦ ለማ ባይሆን በጥቂጡ በአማርኛ ቢናግሩ? …. እስኪ ምን አለበት? … ብስክስክ አደረገኝ”…ለካስ ራያ ማለት በኦሮምኛ ወታደር ተጋዳላይ ማለት ነው አሉ። እነዚህ የተከዜ ማዶ ሰወች ደግሞ እንዴት አድረገው ይችን “ራያ” የምትለዋን የአቶ ለማ ቃል ምሽቅርቅሯን አወጧት መሰላችሁ?  “ዋይይይ አማራ ምስኪኒ አይት ሎማ መጎርሳ ራያ ኦሮሚያ ዝኮነ በልሁ” … እያሉ የኔ ቢጤውን ደሙን ባያፈሉትም ሸግ አድርገውታል። እዚሃር ይይላቸው እንጅ ሌላ ምን ይባላል። ==================================================================================================

ያልተነካ ግልግል ያውቃል ነው ነገሩ።  ሁላችንም ስንወለድ እብዶች ነን … አንዳንዶቻችን ግን እንደአበድን እንሞታለን “We are all born mad. Some remain so” ብሎ ነበር ቤኬት እንዲህ እንደኔ መያዠያ መጨበጫ የጠፋው ግዜና። እንዲህ እንደአበድን እንዳንሞት እንደየእምንታችን የፈጠረን አምላክ ይርዳን። አሜን!!! ይረዳናል። የሚተወን አይመሰለኝም። ቢያንስ ለራሱ ሲል። ፈጣሪ እኛን  እርስ-በርስ አጠፋፍቶ ካጠፋን ሌላው ቢቀር ተእስላም ክርስቲያኑ እንደኛ ፈርቶ የሚያመልከው ፍጡር የሚያገኝ አይመስለኝም። ማን እንደኛ ይሰግደለታል? ማንስ ነው ሮመዳንን-ከሁዳዴ ሰርክ አንጀቱን አስሮ የሚጾምለት? ከኛ ውጭ ማንንም አያገኝም!  ፈረንጆቹ እኮ አብያተክርስቲያኑን ሁሉ የቆነጃጀት ገብያ አድርገውለታል። እኔ እንደሚመሰለኝ ፈጣሪ እንደኛ  እብደት አና ስራ ቢሆን ኑሮ እስከአሁን እርስ-በርስ  አጨፋጭፎ አጥፍቶን ነበር። ለራሱ ሲል ይሄው እስካሁን አድርሶናል። አሁን አሁን ግን “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥም” ያለ ይመስለኛል። እውነቱን ነው የትእግስትም ልክ አለው። የእዮብን ትግስት ከአማራ ላይ ማንሳቱን ሳይ ለመጨረሻው መጀመሪያ “ምልክት ይሆን እንዴ?” ስትል ነፍሴ ጠረጠርች። ጥርጣሪው ከስጋ እንጅ ከነፍስ ከሆነ ደግሞ የእውነትነቱ ሸህሬታ ከፍ ያለ ይመስለኛል። ለራሱ ሲል እስካሁን ያቆየን ጌታ ያውቃል በሚለው ተስፋችን እንሰንቃት …  እንዲረዳን ግን እንረዳው።

ዘረኝነት የሚሉት ነቀርሳ በመካከላችን ጎርምቷል። ይህንን መካድ አንችልም። ታሪክን ተረት ተረት ትቢያ እንደአለበሰው ሁሉ ፍቅርንም ጥላቻ ደፍቆታል። ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት ቤታችን ሃያሰባት አመት ሙሉ ተዘግቶ በመኖሩ አሁን ስንከፍተው ሸቷል። ምን ሸቷል ብቻ ገምቷልም ጭምር እንጅ። ቀላል ለማንለው ግዜም እንደተግማማን መኖራችን አይቀሬ ነው። እንደገማንም ላንቀር እንደምንችል ማረጋገጫ የለም። እንዲያ ሁኖ ላለመቀረት ግን ተስፋችን ፅኑ ናት። አማራጩ አንድ እና አንድ ብቻ ነው። እራስን ሳይጥሉ ሌሎችንም እንደራስ መውደድ። በርግጥ ፍቅርና መከባበር የሁለትዮሽ mutual ነው። ካለበለዚያ “ግንጥልጌጥ” ይሆናል። ቢሆንም ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር በእጅጉ ያተርፋል። በተለይ እንደሃገር ሲታሰብ በመከባበር ላይ የተመሰረተ ማህበራዊ ፍቅር ከሌለ ሃገር እንደሃገር ይቀጥላል ተብሎ አይታሰብም።===========================================================================================

 እደሚመሰለኝ የትናትናው የአቶ ንጉሱ ንግግር ያለንበትን ሁኔታ አሳምሮ የተረዳ ብቻ ሳይሆን አዕምሮ ውስጥ ሊያቃጭሉ የሚችሉ ጥያቄዎቻችንም ከወዲሁ መልሷል ብንል ማጋነንም መሳሳትም አይሆንም። በሳል ንግግር። የአቶ ንጉሱ ንግግር ወደፅንፍ እየሄደ የነበረውን የታዳሚ ድቫቭ mood ወደማህል ጎትቶ እንዳመጣው ሁላችንም ታዝበናል። አቶ ንጉሱ “የአማራ ህዝብ ወንድም ከሆነው የኦሮሞ ህዝብ ..” ብለው ገና ንግግራቸውን ሳይጨርሱ ታዳሚው “ወንድም” የምትለዋን ቃል ሰለሰማ ብቻ “ይደገም! …. ይደገም! …. ይደገም! …” ሲል አዳራሹን አናወጠው። በርግጥም የአማራ ህዝብ ለኦሮሞ ህዝብ በደምና በስጋ የተዋሃደ ወንድሙ ነበር። ዳሩ ላለፉት 27 አመት እውነታው ተገልብጦ ሃቁን ዳዋ ስለዋጠው የደረሰው ጉዳት እጅግ አሰቃቂ ነበር። ለአቶ ንጉሱ ንግግር በታዳሚው ከተገለፀው ስሜት የተረዳነው ነገር ቢኖር የኦሮሞ ህዝብ “ወንድም” እንደናፈቀው ነው። ከወንድሙ ከአማራ ህዝብ የለያዩት እንዚያ የተከዜ ማዶ “የቀን ጅቦች” እጅግም እንደአናደዱት ነው። “ወንድም” ሲሉ አቶ ንጉሱ! … “ድገሙልኝ” አለ የኦሮሞ ወጣት። ሰው እኮ ደገምልኝ የሚለው የሰማውን ነገር ማመን ሳይችል ቀርቶ ዳግም ለማረጋገጥ ሲፈልግ ነው። እናም ሲደገመለት የልቡ ይደርሳል። የትናቱ የአቶ ንጉሱ ንግግር ለኦሮሞ ወጣት የልቡን አድርሶለታል።

======================================================================================================

አቶ ንጉሱ ላለፉት ሃያሰባት አመታት ተዘግቶ የነበርውን የቤታችን ሳንቃ በትናትናው ንግግራቸው ትንሽ ገርበብ አድርገው መክፈት በመቻላቸው የነበርውን ግማት በመጠኑም ቢሆን ማስተንፈስ ችለዋል። በራፉ ተንገርብቧል። ሽታውም እንደአለ ነው። የተንገረበበውን በራፍ ከፍቶ እውስጡ የታሸገውን ግማታም ሽታ ማባረር የሚቻለው በዕንደትናቱ አይነት የአቶ ንጉሱ ንግግር መሆኑን የትናቱ መድረክና ታዳሚ ድንቅ ምስክር ነው። “ወንድም”! የምትለዋን ቃል ሲሰማ ..”ይደገም! … ይደገም! …ይደገም!” አለ ልቡ እሰከሚጠፋ።  ምን ያድርግ “እትብቱ ተቆርጦ ጥርሱን እስከሚነቀል ድረስ ያደገው .. አማራ ጠላትህ ነው!” እየተባለ ነው። እድሜ ለነተስፋየ ገብረዓብ:: ለነመለስ ዜናዊ። ለነበረከት ስመዖን:: ለነሌንጮ ለታ። ላለፈው ሃያሰባት አመት ሰምቶት የማያውቀውን ቃል በአቶ ንጉሱ ሲሰማ …የኦሮሞ ወጣት ልቡ በሃሴት ፈነጠዘች።

አቶ ንጉሱ ጥላሁንን አለማማሰገን አይቻልም!

እዚሃር ከእርሰዎ ጋር ይሁን ጌታየ!                      ===================================================================

x

Check Also

ብዙ ጊዜ እውነትን ውሸት ይቀድመዋል-የሺሃሳብ አበራ

ብዙ ጊዜ እውነትን ውሸት ይቀድመዋል፡፡ እውነት ዳተኛ ናት ወይም ቶሎ አትገለፅም፡፡ እውነት ቶሎ መገለፅ ባለመቻሏ ምክንያት በዓለም ...