የአማራ ገበሬዎች አሁንም ከሱዳን ሰራዊት ጋር ዳር ድንበር ለማስከበር እየተዋደቁ ነው | ክርስቲያን ታደለ

(ክርሥቲያን ታደለ ፀጋዬ)
*****
፩ የአማራ ገበሬዎች አሁንም ከሱዳን ሰራዊት ጋር ዳር ድንበር ለማስከበር እየተዋደቁ ነው። የአገር መሪውና የክልሉም ርዕሰመስተዳደር አልያም የሚመሩት ድርጅትና የፀጥታ ኃይል ለገበሬዎቹ ሊደርስ አልቻለም። መኪና ተቃጠለ ብሎ ሲወራጭ የነበረው ገዱ አንዳርጋቸው በመኪናው «ቃጠሎ» ግርግር ስለሞተው አማራ ወጣት፣ስለተጎዱ ሰዎችም ሆነ የሱዳን ወታደሮች ማሳቸው ላይ ስለሚገድሏቸው የአማራ ገበሬዎች ትንፍሽ አላለም። የአማራ ነፍስ ለእነሱ ከመኪና የረከሰ ከዳንኪራም ያነሰ ነው።

፪ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን የእምዬ ምኒልክን ስም ጨምሮ ስለምን የአማራ ነገስታትን ስም አነሳ ብለው የአማራ ነገስታት ስም መነሳቱ ለአገር ግንባታ እና ለዐብይ አሕመድ የ«መደመር» ኃለዎት ስጋት መሆኑን በርካቶች ጽፈው አነበብሁ። የምንደመረው አማራነትን ለማጥፋት ነበርወይ? የአማራ ነገስታት ታሪክ የአማራነታችን አስኳል መሆኑ ተዘነጋ ወይ? አማራ በወፈሰማይ ስሪት እንዲሁ ሲመራ የነበረ ሳይሆን ከዘመን በፊት መንግሥታዊ ሥርዓት የነበረ ታሪክ ፀሐፊው አርስቶትል «ኢትዮጵያ ቅድመዓለም መንግስት ወጣኝ፤ ቅድመዓለም ሀገረ መንግሥት ነች» እንዲል ያስቻለው እኮ የነገስታት አባቶቻችንን ደማቅ ታሪክ መርምሮ ነው። ይኸ ታሪካችን ለኢትዮጵያ እንደአገር ለመላው ኢትዮጵያውያንም እንደሕዝብ የኩራት ምንጭ ቢሆን እንጂ ምን ስላጎደለ ነው አይነገር፤ አይወራ የሚባለው? የእምዬ ምኒልክ ስም በቆረቆራትና የአማራ ርስተምድር በሆነቺው አዲስ አበባ በክብር ያልተወሳውስ የት ሊነገር የት ሊዘከር ኖሯል? አማራ ታሪኩን ያድሳል ስንል የቀደመ እኛነታችን ተገቢውን ክብር እንዲያገኝ፤ እንኳንስና በሕይወት ያሉ የታሪካችን አስኳል የሆኑ በቀደመ እኛነታችን የነበሩ አገር ገንቢዎችን መልካም ስም ሕጋዊ ከለላ እንዲያገኝ፣ ይህን ተላልፈው በሚገኙ ላይም ተገቢውን የሕግ ቅጣት እንዲያገኙ እናደርጋለን ማለት ነው። የአማራን ነገስታቶች ክብር ማጉደፍ ወንጀል ሆኖ በሕግ የሚያስጠይቅበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። የአማራ ጠልነት ንግግር ነው። በመላው ዓለም ፀረ–ሴሜቲክ ንግግር ተብሎ ህግ ፊት እንደሚያስቀርበው ሁሉ አማራ ጠል ንግግሮችና ማናቸውም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ነገሮች በሕግ ገደብ የሚደረግበት ቀን ሩቅ አይሆንም።  ፫ ይሄ መልዕክት መሐል ሰፋሪ ለሆኑ በሐሳዊ የኢትዮጵያ አንድነት ትርክት ለሚነሆልሉ፤ አማራዎች ነው። ከላይኛዎቹ ሁለት ነገሮች ምን ተማራችሁ? ቆይ ኢትዮጵያዊነት መንፈስ ነው እንዴ? ማለቴ ሉዓላዊነት የሌለበት የዜግነት ክብር አለ? አማራን ያገለለና የነጠለ ሥርዓት መደገፍ ለእናንተስ ይመጥናል ወይ? አማራው በአስቃቂ ሁኔታ እየተገደለ፣ ተፈናቅሎ መድረሻ እንኳን አጥቶ በዚህ ክረምት ሰማይን ጣራ አድርጎ እየኖረ፣ አሁንም ድረስ የአማራ ወጣቶች የእስር ማደኛ እየወጣባቸው፣ አሁንም ድረስ አርሶአደሮች ማሳቸው ላይ በሱዳን ሰራዊት እየተገደሉ፣…ምን አይነት ኅሊና ነው እነዚንና እነዚን መሰል ግፎች እንዳልተፈጠሩ የሚያልፈው? ምንስ አይነት ስነልቦናዊ ስሪት ነው እንዲህ የሚያደርገው? ይህ እኮ እናትን አስገድዶ ለሚደፍር ወሮበላ ጉሮወሸባዬ ከመጨፈር አይተናነስም! ይህ እኮ ልጅን አስገድዶ ለደፈረ የሰፈር ጎረምሳ ሚስቴንም ድገምልኝ የማለት ያህል ነው።

፬ እንደምን አደራችሁ ግዮናውያን! የእናንተ ወንድም ያረገኝ፤ የእናንተ ዘመን ተጋሪ ያደረገኝ፤ የእናንተ ሕልም ተጋሪ ያደረገኝ አምላከ ዮቶር ይመስገን፤ እኔ ደህና ነኝ። እንደግዮን ፈረሰኛ ውኃ እየተምዘገዘገ ባለው የአማራ ብሔርተኝነት ላይ በርካቶች መናኛ አስተያየት እየሰጡ እንደሆነ ታዝበናል። ወንድም ጋሻው መርሻ እንዳለው «ዝሆን ለማደን የወጣ ሰው በጥንቸል አይታኮስም»ና ትኩረታችን ሁሉ በአማራ ሕዝብ የኅልውና ጥያቄዎች ላይ እንዲሆን ወንድማዊ መልዕክቴ ነው።

አማራ በልጆቹ ትግል ታሪኩን ያድሳል!

x

Check Also

Team Ambachew – ሚኪ አማራ

perfect leader ማግኘት አንችልም ነገር ግን እኛ ፐርፌክት ማድረግ እንችላለን፡፡ አሁን ተወደደም ተጠላም ዶ/ር አምባቸዉ ...