አብይ በዋሽንግተን ዲሲ | ወንድይራድ ሃ/ገብርዔል

አብይ በዋሽንግተን ዲሲ

Image result for Abiy in DC

“አረቂ ቤት ሆኘ አልሞትም”

በርግጥ ጠቅላይ ሚንስትሩን አለማድነቅ አይቻልም። የጭንቅላታቸው ብሩህነትም ሆነ ቅኝታዊ ፍጥነት ሳያቀባብል ጭምር የሚተኩስ quick witted እንደሚባለው አይነት ነው። አንደበተ ርዕቱ ብቻ ሳይሆኑ የምላሳቸው ስለትም(sharpness) ጭምር  የጉድ ነው።  እንዲህያለውን ሰው ፈረንጆቹ –“Can speak under the water (እሱ! እሱማ ውሃ ወስጥ ሰምጦም ቢሆን ይናገራል)“ ይሉታል። ሰውየውን ንባብ አጎልምሷዋል። ታዲያ ይህንን እውነታ መቀበል ያቃታቸውና የጠቅላይ ሚንስትሩን አኳኋን ( ብራኬቱን በማፍረስ የመደመር ፖለቲካ ፍልስፍናን) ያልወደዱት ጠላቶቻቸው፡ እንደሳቸው አገላለጽ  “የቀን ጅቦቹ” እርሳቸውን ያሳነሱ እየመሰላቸው “(ሰባኪው፡ካህኑ፡ ቄሱ) ጠቅላይ ሚንስትር Pastor” ሲሉ በወንጌል ወርድና ቁመና ሊለኳቸው ሲሞክሩ ይስተዋላል::  በርግጥ አገላለጹ ለጎሪጥ ሆነ እንጅ፡ ቀጥ ያለ ቢሆን ኖሮ ሰውየው “ ካህንም እረኛም Pastor and Pastoral መሆናቸውን ሁላችንም ታዝበናል። ኧረ እንዴያውም ለአንዳንዶቹማ ዶ/ር አብይ እንደመሲህም ጭምር ይቆጠራሉ። እንደክርስቶስ። እኔ ግን አንድ ነገር እላለሁ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለክርስቶስ በንብረትነት ተላልፎ የተሰጠ Christ hood የሚመስል ስብእና አይቸባቸዋለሁ:: መቸም ይሄ ደግ ነገር ነው። የፈጣሪ ስም ሲነሳ አፉን ከፍቶ ከሚሳለቀ መሪ አውጥቶ አይኑን ጨፍኖ ለጸሎት ወደሚተጋ መሪ ለአሸጋገርን አላህ (ልዑል እግዚአብሄር) ክብር ምሰጋና ይሁን! አሜን ማለት ተገቢ ነው። እንዲህ አላህን ስናመሰግን አሜን! የማይል ሰው ቢኖር ያ! ሰው ወይ “የቀንጅብ” ነው። ካልሆነም ደግሞ እስካሁን ሳይደመር እየተንገዋለለ ያለ የቀኖቹ ጅቦች ወንድም ነው።

ወደ ዲሲ እንሂድ!

 መቸም ይችን ሁለት ቀን ዲሲ በጭንቅላትዋ ቆማ ተመልክተናታል። ዲሲ የጉድ ሃገር ናት። ዲሲ የነታማኝ በየነ ግዛት ናት። ዲሲ ሁሉም አለ። በርካታ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ድርጅቶች፡ አብያተክርስተያናት እና መስጊዶች፡ እድሜ ለቀደመው ጠቅላይ ሚንስትር ታምራት ላይኔ እንጅ ዲሲ ሶስት ሲኖዶስ ነበራት። ቢያንስ እስከትናትና ድረስ። “ህጋዊው” “ህገ-ወጡ” “ገለልተኛው”። ገለልተኛ ይባል የነበረውን ሲኖዶስ አቡነ በርናባስ “ጋለሞታ” ሲሉ ነበር የሚጠሩት። እውነታቸውን ነው። ጋለሞታስ ጋለሞታ ነብሩ። ከእውነት ተፋተው በእዉነት ጎን መቆምን ያልደፈሩ ጋለሞታ ክርስቲያኖች። ታምራት ላይኔ ዛሬ የየሱስ ባርያ ሁነዋል። ህጋዊውን ሲኖዶስ በማፍረሳቸው ተጸጽተው አቡነ መርቆርዮስንም ይቅርታ ጠይቀዋል ሲባል ሳልስማ አልቀረውም። ጅጅጋ ሄደው “አማራ ሽርጣም እያለ ሲሰድብህ ኖሯል፡ አሁን ታሳየኛለህ ብለው” ሲያስጨፈጭፉት የኖሩትን አማራን ግን ይሄው እስከዛሬ ይቅርታ እንኳን አልጠየቁትም።  የምድሩን ብንተወው እንዲህ ያለው ሃጢያት ለዘላለም ሂወት ያበቃቸዋል ብየ አላምንም። ወጣም ወረደም እርሳቸውም ተደምረዋል። ከነደማቸው።

ዲሲ እንደዚህ ናት። ዲሲ ከተናትናው አንድ አማራ እሰከ የኦሪት ዘመኑ ኢህአፓ ከ67ቱ መኢሶን እስከ ግንቦት 7ቱ አርበኞች፡ ዲሲ ባለብዙ ጓዝ ናት። ዲሲ እና አባይ ያልተሸከሙት ነገር የለም።  እልፍ አላፍ ሊቀመኳሶች እና ሊቀመኳሲት፣ ሃያሲያን፣ ብቻ አይነተኛው ሁሉ በየአይነቱ ዲሲ ላይ ይገኛል። አንድ አባት “ከፍሎሪዳ ነፋስ ከዲሲ ምላስ ይሰውራችሁ” ሲሉ ከሰማሁ ወዲህ ዲሲን በሙሉ አይኔ አይቻት አላውቅም። ከባትሪ አሲድ የበረታ አሉባልታ ዲሲ ላይ ይመረታል።  እንግዲህ ይሄ ሁሉ ነው በዲሲ ከዶ/ር አብይ ጋር አንድ አዳርሽ ውስጥ የተገኘው። በርግጥ ይገርማል። የማይገረም ካለ እርሱ ለማስገረም እንጅ ለመገረም የተፈጠረ አደለም። ዲሲ እንደዚህ ናት።

ነገርን ነገር እየነካካብኝ በውል ሳላስበው እንዲህ አሰብኩ። አይበለው እና ብየ ጀመርኩና “ ጠቅላይ ሚንስተር ሆነው የተሰየሙት አቶ ደመቀ መኮንን ሆነው ቢሆን ኖሮ” ዲሲ ለአብይ እንደዘመመችው ለደመቀ ታረገድ ነበር ወይ”? የሚል ጥያቄ አዕምሮየ ላይ ተሰነቀረብኝ። ይሰንቀር አባቱ እና  መልሸ ደግሞ እንኳንም የሰይጣን ጀሮ አልሰማ ስል እንዲህ ያለው ጸረ መደመር አጉል ሃሳብ ከዚህ በላይ እንዳያንገላታኝ አሽቀንጥሬ ጣልኩት። መልሶ ደግሞ ብቻ አማራ ደግ ህዝብ ነው አለና ታረቀኝ። ዛሬም እንደአማራ እየሞተ እንደኢትዮጵያ ሲጨፍር ሳየውፈጣሪ ሆይ አማራን ሰትፈጥር እውነት እንዲያው ትንሽ ድክም ብሎህ እረፍት ላይ ሆነህ ይሆን እንዴ? ”? ሆኖ ነው እንጅ ታዲያ ሰው ሁሉ መቀመጫውን ሳይሸፍን እራሱን የተከናነበው። ወድጅ አይመሰላችሁ። አሰቦት ከወልቃይት እየተፈራረቁ ቢያዉኩኝ እንጅ። የአማራ እና የኢትዮጵያ ፍቅር ልዩ ነው። የተባረከ ህዝብ። እውነት ለመናገር እኮ ጠቅላይ ሚንስትሩን እንደ አማራ ህዝብ የደገፋቸው የለም። የወጡበት ነገድ ሳይቀር የጎሪጥ እያያቸው አደለም እንዴ? ዳውድ ኢብሳ ምስክሬ ናቸው። የአማራ እናት ውላ ትግባና ጠቅላይ ሚንስትሩን አማራው ወዶአቸዋል። 50 ሚልዮን አማራ ከወደዳቸው ፍቅሩን ያዝለቀው እንጅ ወደቀው አይወድቁም።

ወደ ዲሲ እንመለስ!

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ እና ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በዋሽንግተን ዲሲ። አንዲት የተከበሩ ኢትዮጵያዊት እናት ለኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስተር ዶክተር አብይ አህመድ በፍቅር የተደመረው የእናትነት አንጀታቸው እየተላወሰ

 “ልጀ እባክህን ተጠንቀቅ፡ የቀን ጅቦቹ አንተንም እንዳይበሉህ፣ እራስህን ጠብቅ ወዲያ ወዲህ ሱክ ሱክ ስትል አራት አይንህን አብረተህ ይሁን፡ የቀን ጅቦቹ እጅ  እንደ ቀትር እባብ ረዥም ነው፡ አሁን ባለፈው ከኢሳያስ ጋር አዋሳ የሄድክ ግዜ እየተጓዝክ የነበረበት መኪና ሳይቆም በር ከፍተህ መውጣትህ ተገቢ አደለም፡ እናም እባክህ ልጀ በዚህ ግዜ አንተ ኢትዮጵያን ከምተፈለጋት በላይ ኢትዮጵያ አንተን አሳልሳ ትፈልገህ አለች፡ እራስህን ጠብቅ”

 ሲሉ ምክር ቢጤ በእናትነት ተግሳጽ ሰጡት። በእውነት አንጀት ይበላሉ። ሳስተውለት እኮ ነው።

 ጠቅላይ ሚንስተር አብይም በእናትነት ፍቅር የቀረበለት “የኑርልን” ምክር የልጅነት አንጀቱን እያንቦጫቦጨው፡ አላንቦጨቦጨውም ማለት አየቻልም።

 “አይዞዎት እናቴ፡ ከሞትኩም አረቂቤት ወይንም ጫት ቤት ሆኘ አልሞትም” ……………. አላቸው።

 እንደሃየሎም አረያ (ይቅርታ “ሜጀር ጄኔራል”) መለኪያ እያጋጨው አረቂቤት እንደተጎለትኩ አየገሉኝም ማለቱ ነው። ዶር አብይ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሚጠየቃቸውን ጥያቄዎች ሲመልስ የህወሃት ሰወችን ሰንኮፍ መዥግሩን ከመንቀል አልቦዘነም።

 “ከሞትኩም እንደ አጼ ቴዎድሮስ የተበተነችውን ሃገሬን እየሰበሰብኩ ቀዳዳዋን እየሰፋው እንጅ እንደ ሃየሎም አረቂ ቤት ተጎልቸ የቆንጆ መቀመጫ አየኔን ሲያዞረው ምረቄ ባፌ እየሞላ አደለም” ሲል ነው ለደህነነቱ የሰጉትን እናት ያረጋጋቸው።

አረቂ ቤት የሚወደውን እያደረገ የተገደለዉን ሃየሎምንም ሆነ የተበተነች ሀገር ሲሰበሰቡ በጀግንነት የወድቁትን የአጼ ቴዎድሮስን ነፍስ ይማር! የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ሆኖ እንጅ ሁለቱም የአዲት እናት የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው።

መች በዚህ ቆመና ነው!

 ዶ/ር አብይ …….. “ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ማለት የኢትዮጵያ የቁርጥቀን ልጅ ናቸው። ሃገራችን ካፈራቻቸው የህግና የዲፕሎማሲ ሰወች መካከል ኮሎኔል ጎሹን የሚተካከል የለም”

ሲል ካወደሳቸው በኋላ ……….

 “ኮሎኔል ጎሹ እዚህ አዳራሽ ውስጥ ካሉ እባከዎ ሰላም ልለዎ እፈለጋለሁ”

ሲል ድምጹን ከፍ አደርጎ ተጣራ።

 “እንዴታ! አለሁ እንጂ ሲሉ”

ኮሎኔል ጎሹ ከተቀመጡበት ወንበር ተነስተው ወደ ዶክተር አብይ ተራመዱ። ዶር አብይ ግማሽ መንገድ ድረስ ሄዶ ኮሎኔሉን ተቀበላቸው። እቅፍ አደርጎም ተከሻቸውን እየደባበሰ ሳማቸው። ኮሎኔሉም እንደዛው።

  ቀጠለና …….

“ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ማለት ከቀደመው የመንግስቱ ሀለማሪያም መንግስት ለሰራ ወደአሜሪካ እንደመጡ በተቃዎሞ አፈንገጠው ሲቀሩ መንግስት ለውሎ አበል የከፈላቸውን ገንዘብ ከነመመለሻ ትኬቱ ለኢትዮጵያ መንግስት መለሰው ያሰረከቡ ታማኝ የኢትይጵያ ልጅ ናቸው”

 ሲል ሰምተን የማናወቀውን ገድል መሰከረላቸው።

 በእውነት የኮሎኔሉ ታማኝነት እጅግ የሚገርም የሚያሰመሰገንም ጭምር ነው። ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚሁ አሰታከኩና ታዲያ

 “ዛሬ ዛሬ መሰንበት ደግ ነው! እነኮሎኔል ጎሹን የመሰሉ ታማኝ መሬዎች በጠቀመጡበት ወንበር የእናታቸውን መቀነት እየፈቱ የሚሰርቁ መዥገሮች ተሰየሙበት”

ሲሉ የሀወሃትን ሌቦች አሸማቅቀው ገረፏቸው።  በርግጥ እንደስጦ ነው ያሰጧቸው። አባይ ጸሃየ ይህንን ሲሰማ ምን ተሰምቶት ይሆን? ለነገሩ ምንም ላይሰማው ይችላል። ከህሊናው የተፋታው የእናቱን መቀነት መፈታት በጀመረበት ጊዜ ነው።

በርግጥ ጠቅላይ ሚንስትር አብይን አለማድነቅ ግብዝነት ነው። ሰዉየው የዋዛ አደሉም።

ይቀጥላል! ዲስ መች እንዲህ በዋዛ!

አብይ በዋሽንግተን ዲሲ በርግጥ ጠቅላይ ሚንስትሩን አለማድነቅ አይቻልም። የጭንቅላታቸው ብሩህነትም ሆነ ቅኝታዊ ፍጥነት ሳያቀባብል ጭምር የሚተኩስ quick witted እንደሚባለው አይነት ነው። አንደበተ ርዕቱ ብቻ ሳይሆኑ የምላሳቸው ስለትም(sharpness) ጭምር  የጉድ ነው።  እንዲህያለውን ሰው ፈረንጆቹ --“Can speak under the water (እሱ! እሱማ ውሃ ወስጥ ሰምጦም ቢሆን ይናገራል)“ ይሉታል። ሰውየውን ንባብ አጎልምሷዋል። ታዲያ ይህንን እውነታ መቀበል ያቃታቸውና የጠቅላይ ሚንስትሩን አኳኋን ( ብራኬቱን በማፍረስ የመደመር ፖለቲካ ፍልስፍናን) ያልወደዱት ጠላቶቻቸው፡ እንደሳቸው አገላለጽ  “የቀን ጅቦቹ” እርሳቸውን ያሳነሱ እየመሰላቸው “(ሰባኪው፡ካህኑ፡ ቄሱ) ጠቅላይ ሚንስትር Pastor” ሲሉ በወንጌል ወርድና ቁመና ሊለኳቸው ሲሞክሩ ይስተዋላል::  በርግጥ አገላለጹ ለጎሪጥ ሆነ እንጅ፡ ቀጥ ያለ ቢሆን…

Review Overview

User Rating: 4.5 ( 1 votes)
x

Check Also

የአማራ ክልል ከፍተኛ የፀጥታ ክትትል ችግር አለበት – ሚኪ አማራ

⚡️ክልሉ እንደ ሃብታም ቤት ተበርግዶ (የሃብታም ቤትስ አንዳንዴ ይዘጋል) ሲፈልግ ከባድ መሳሪያ፤ ሲፈልግ ታንክ ፤ሲፈልግ ...